2 Chronicles 28

የይሁዳ ንጉሥ አካዝ

28፥1-27 ተጓ ምብ – 2ነገ 16፥1-20 1አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ፣ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር እንዳደረገው እንደ አባቱ እንደ ዳዊት አላደረገም። 2በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በኣሊምን ለማምለክም የተቀረጹ ጣዖታትን ሠራ። 3እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት ያስወገዳቸውን አሕዛብ ልማድ በመከተል፣ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ዐጠነ፤ ወንዶች ልጆቹንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። 4በኰረብታ መስገጃዎችና በተራሮች ዐናት ላይ፣ በየዛፉም ጥላ ሥር መሥዋዕት አቀረበ፤ ዕጣንም ዐጠነ።

5ስለዚህ አምላኩ እግዚአብሔር ለሶርያ ንጉሥ አሳልፎ ሰጠው፤ ሶርያውያንም ድል አደረጉት፤ ከሕዝቡም ብዙዎቹን ምርኮኞች አድርገው ወደ ደማስቆ ወሰዷቸው። ደግሞም ለእስራኤል ንጉሥ ዐልፎ ተሰጠ፤ እርሱም ከባድ ጕዳት አደረሰበት። 6ይሁዳ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ መቶ ሃያ ሺሕ ወታደሮች ገደለ። 7ጦረኛው ኤፍሬማዊ ዝክሪም የንጉሡን ልጅ መዕሤያን፣ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ የሆነውን ዓዝሪቃምንና ለንጉሡ በማዕረግ ሁለተኛ ሰው የሆነውን ሕልቃናን ገደለ። 8እስራኤላውያንም ከገዛ ወገኖቻቸው ሁለት መቶ ሺሕ ባለ ትዳር ሴቶችን፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ማረኩ፤ እንዲሁም እጅግ ብዙ ምርኮ ይዘው ወደ ሰማርያ ተመለሱ።

9ዖዴድ የተባለ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚያ ስለ ነበር፣ ሰራዊቱ ወደ ሰማርያ በተመለሰ ጊዜ ለመቀበል ወጣ፤ እንዲህም አላቸው፤ “የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ይሁዳን ስለ ተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣችሁ፤ እናንተ ግን እስከ ሰማይ በሚደርስ ቍጣ ፈጃችኋቸው። 10አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ወንዶችና ሴቶች፣ ባሪያዎቻችሁ ልታደርጓቸው ትፈልጋላችሁ፤ እናንተስ ብትሆኑ ኀጢአት ሠርታችሁ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አልበደላችሁምን? 11እንግዲህ ስሙኝ፤ የእግዚአብሔር አስፈሪ ቍጣ በእናንተ ላይ ነድዷልና፣ በምርኮ ያመጣችኋቸውን ወገኖቻችሁን መልሷቸው።”

12ከዚያም ከኤፍሬም መሪዎች ጥቂቶቹ የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፣ የምሺሌሞት ልጅ በራክያ፣ የሰሎም ልጅ ይሒዝቅያ፣ የሐድላይ ልጅ ዓሜሳይ ከጦርነቱ የተመለሱትን በመቃወም፣ 13“እነዚህን ምርኮኞች እዚህ ማምጣት አልነበረባችሁም፤ አለዚያ እኛ በእግዚአብሔር ፊት በደለኞች እንሆናለን፤ በኀጢአታችንና በበደላችን ላይ ሌላ ልትጨምሩ ታስባላችሁን? በደላችንማ ቀድሞውኑ በዝቷል፤ ቍጣውም በእስራኤል ላይ ነውና” አሉ።

14ስለዚህ ወታደሮቹ በሹማምቱና በጉባኤው ሁሉ ፊት ምርኮኞቹን ለቀቁ፤ የተማረከውንም ዕቃ መለሱ። 15በስም የተጠቀሱ ሰዎችም ምርኮኞቹን ተረክበው ዕራቍታቸውን ለቀሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሷቸው፤ ልብስና ጫማ፣ ምግብና መጠጥ ሰጧቸው፣ በቅባትም ቀቧቸው፤ የደከሙትንም ሁሉ በአህያ ላይ አስቀመጧቸው። ከዚያም ወገኖቻቸው ወደሚገኙባት የዘንባባ ከተማ ተብላ ወደምትጠራው ወደ ኢያሪኮ ወስደዋቸው፣ ወደ ሰማርያ ተመለሱ።

16በዚያን ጊዜ ንጉሡ አካዝ ወደ አሦር ንጉሥ ልኮ ርዳታ ጠየቀ፤
አንድ የዕብራይስጥ ቅጅ፣ የሰብዓ ሊቃናትና የሱርስቱ ቅጅ እንዲሁም (2ነገ 16፥7) ከዚህ ጋር ይስማማል፤ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ትርጕሞች ግን ነገሥታት ይላሉ።
17ኤዶማውያን እንደ ገና መጥተው በይሁዳ ላይ አደጋ በመጣል ምርኮኞችን ወስደው ነበርና። 18ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በየኰረብታው ግርጌና በይሁዳ ደቡብ ያሉትን ከተሞች በመውረር ቤትሳሚስን፣ ኤሎንን፣ ግዴሮትን፣ ሦኮን፣ ተምናን፣ ጊምዞንና በአካባቢአቸው የሚገኙትን መንደሮች ሁሉ ያዙ፤ ተቀመጡባቸውም። 19የእስራኤል
በዜና መዋዕል ካልዕ መጽሐፍ ተደጋግሞ እንደ ተጠቀሰው ይህ ይሁዳ ነው።
ንጉሥ አካዝ ክፋትን በይሁዳ ምድር ስላስፋፋና ለእግዚአብሔርም የነበረውን ታማኝነት በከፍተኛ ደረጃ ስላጓደለ፣ እግዚአብሔር ይሁዳን አዋረደ።
20የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ወደ እርሱ መጥቶ ነበር፤ ሆኖም ችግር ፈጠረበት እንጂ አልረዳውም። 21አካዝ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ከቤተ መንግሥቱና ከመሳፍንቱ ጥቂት ዕቃዎች ወስዶ ለአሦር ንጉሥ ሰጥቶ ነበር፤ ይህም አልረዳውም።

22ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜም፣ ለእግዚአብሔር የነበረውን ታማኝነቱን ከምን ጊዜውም ይበልጥ አጓደለ፤ 23እርሱም “የሶርያ ነገሥታት አማልክት እነርሱን ስለ ረዷቸው፣ እኔንም ይረዱኝ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ” ሲል እርሱን ላሸነፉት የደማስቆ አማልክት መሥዋዕት አቀረበ።

24አካዝ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ሁሉ አንድ ላይ ሰብስቦ ወሰደ
ወይም ሰበረ ተብሎ መተርጐም ይችላል።
የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሮች ዘጋ፤ በኢየሩሳሌምም በየአውራ ጎዳናው ማእዘን ላይ መሠዊያ አቆመ።
25በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት መሥዋዕት የሚያቃጥልባቸውን የኰረብታ መስገጃዎች ሠራ፤ በዚህም የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ አነሣሣው።

26በአካዝ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ተግባርና አካሄዱ ሁሉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፏል። 27አካዝ እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በኢየሩሳሌምም ከተማ ተቀበረ፤ የተቀበረው ግን በእስራኤል ነገሥታት መካነ መቃብር አልነበረም። ልጁ ሕዝቅያስም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።

Copyright information for AmhNASV